አንዳንድ ቀን ደርሶ ይደብረኛል ፤ ለድብርቴ መፍትሔ ደግሞ ወክ ማድረግ ወይም መጻፍን እመርጣለሁ ።

ዛሬም ድብርቴ ድንገት ተነሳብኝና እራሴን ከግቢ አስወጥቼ ወደ ፈርንሳይ ለጋሲዮን መራሁት ። ብዙውን ጊዜ አዲስ አበባ ከሰፈር ሰፈር ስሄድ ትራንስፖርት አልጠቀምም ። ታክሲ መጠቀም ገንዘብ ከማባከኑም በላይ ብዙ በእግሬ ብሄድ የማገኛቸውን ጥቅማ ጥቅሞች ያሳጣኛል ። በእግሬ ጉዞን እያጧጧፍሁት ሳለ እጅግ ደስ የምትል ህጻን ልጅ በእይታየ ውስጥ ገባች ። አንዳንዴ ቀልቤ የወደዳቸውን ህጻናት ቀርቦ ሰላምታ መስጠት ፤ ጥያቄ መጠየቅ እና የማውቀውን መንገር ደስ ይለኛል ። ህጻናት ከዚህ ዘመን ወጣቶች ይበልጡብኛል ፤ አስተሳሰባቸውን ሳይቀይሩ ልብሳቸውን እና ስብዕናቸውን ቀይረው በእብደት ዓለም ወስጥ ከሚማቅቁ ፤ ይሉኝታቸውን ሽጠው ፤ የምዕራባውያንን ባህል የሚያንጸባርቅ ልብስ እና ባህል ከሚሸምቱ ጎልማሳዎች ህጻናት ይበልጡብኛል ።

መንገዴን ገታ አድርጌ

“ሚጡካ እንደምን አለሽ ? ” አልኳት ተደግፋ ወደቆመችበት መኪና እጄን ለሰላምታ እየሰደድኩ፤

በተወዛገበ ስሜት ሆና “ደ.ደ. ና ” አለችኝ (ስላላወቀችኝ ፍራቻ እየተነበበባት)

“ፈራሽኝ እንዴ ” ብዬ ሳልጨርስ “ማነህ አንተ!” የሚል ደምጽ ከወደኋላዬ አስበረገገኝ ። ዞር ስል ወደ አርባወቹ የሚጠጋ እድሜ ያለው ሰው አሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ እያየኝ ነው።

ድንግጥ አልሁ ።

“ታውቃታለህ ልጅቷን ? ምንድን ምንድን ነህ ? “

የሚገለኝ ያክል ተሰማኝ ።

“ይቅርታ እኔ ሰላም ልበላት ብዬ ነው እንጂ አላውቃትም ” አልኩት እየተርበተበትኩ አንድ ርምጃ ወደኋላ ፍንጠር አልኩና ።

“እንዴ! ምናባክ ስለሆንክ ነው የማታቅውን ልጅ ሰላምታ ምናምን እላለሁ የምትለው ? ደደብ ። “

ብዙ የማስረዳው ነገር ቢኖረኝም በዚህ ንዴቱ ከቅጠለ አደጋ ሊያደርስብኝ ይችላል ብዬ ስለሰጋሁ “እሺ በጣም ይቅርታ” ብዬ ማፈግፈግ ስጀምር “የት ነው ምትሄደው ቆይ ማን ልኮህ ነው ስረቅ ተብለህ ነው ? ” አለኝ ወደኔ ጠጋ እያለ ።

ፍራቻ እጅጉን ይንጠኝ ገባ ። የምመልሰው ጠፋኝ ። በመሓል

“ምንድንው ችግር አለ ?” የሚል የሁለት ሰው ድምጽ ተሰማኝ ። ፖሊስ ናችው ።

“ልጄን ሊሰርቅ ሲል እጅ ክፍንጅ ያዝኩት ፤ ሌባ ነው። “

ከዛ በኋላ የተፈጠረው ትዝ አይለኝም ። ብቻ ግን እራሴን ፈረንሳይ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስትያን ፊት ለፊት አግኘሁት ።

የተፈጠረው ነገር ግልጽ ባይሆንልኝም ከ ፖሊሶቹ ና ከባለ ልጁ ግን ሩጬ እንዳመለጥሁ አላጣሁትም ።

አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስትያን ተሳልምኩኝ ። ከመከራ ጥርሶች ሞጭልፎ ያወጣኝ ፈጣሪየን አመስግኜ አቅጣጫዬን ወደ መዳረሻዬ አዞርሁ ።

የሰው ልጅ እንደ አውሬ ስለመተያየቱ ከዚ በላይ ማስረጃ አያስፈልግም ፤ እኔ ባደግሁበት አገር በመንገድ ያገኘሁትን ህጻን ሁሉ ሰላም ብዬ ፤ ስሜ ፤ ጥፋት እያጠፉ ከሆነ እንኳን በተግሳጽ መክሬ ነበር የማልፈው። ቤተሰቡ ማን ይሁን ማን ለሰው ልጅ ሰላምታ መስጠት ነውር ወይም ወንጀል ሊሆን አይችልም ። ያሁኑ ዘመን ትወልድ እየሄደ ያለበት አቅጣጫ አስፈሪ ነው። ከማህበረሰብ የተነጠለና ከቤተሰቡ ወጭ የሃገሩን ማህበረሰብ የማያይ አድርገን አሳድገን ነገ ባህልህን ህዝብህን አክብር ብሎ ለመንገር የሚከብድ ይመሰልኛል ።

የሁለት ዓለም ሰዎች

……………………………………………

ቤተሰብ ጋር ፈታ ስል ቆይቼ ወደ ግቢ መመለስ ነበረብኝና ምሽቱን በእግሬ ገሰገስኩ ። መንገድ ላይ ለብርዱም ፤ ለእንቅልፉም ፈውስ ሊሆን የሚችል ሻይ መጠጣት አሰኘኝ እና ወደ ደሳሳ ሻይ ቤት ጎራ አልኩ ። እጅግ ጠባብ የመንገድ ላይ ሻይ ቤት ።

“ሻይ አለ አደል?” የሚል ጥያቄ አስቀደምሁ ።

“አዎ ቁጭ በል ” አለችኝ የጎጃምኛ ቅላጼ ያላት ሴት ። ገላ የሚያጨንቅ ከመጣበቁ የተነሳ ከሰውነቷ ጋር አብሮ የተሰፋ የሚመስል ሱሪ ቢጤ እና ከላይ ደሞ ከማጠሩ የተነሳ ባጎነበሰች ቁጥር ወገቧን እርቃን የሚያሰቅር ቲሸርት የለበሰች ሴት ናት ። ሻይ እና ዳቦ አዘዝኩ ። ወጥ ያለ እንጀራ እንደማይሆነው ሁሉ ሻይ ያለ ማባያ ደስ ስለማይለኝ እንጅ ሻይ በዳቦ በልቼ ጎን እንደማይሆነኝ አላጣሁትም ።

አቅርባልኝ ጎዳና ጎዳናውን ትመለከት ገባች ። አለባበሷን በቀየረች ምናለ? የሚል ጥያቄ ብልጭ እያለ ያዋክበኝ ያዘ ።

ከመጠጥ እና ከመብሌ ጎን ለጎን በአለባበሷ ዙሪያ ከራሴ ጋር ክርከር ጀመርኩ።

“ሲሆን ሲሆን ለደንበኛ አገልግሎት የሚሰጥ ሰው ሱሪ ባይለብስ ብጎ ነበር ሱሪ ከሆነ ደግሞ ይሄን ያህል መጥበቡ ለምን አስፈለገ ? ምናለ ቀሚስ በትለብስ? ” አልኩኝ ብልቤ።

“ማን ስለሆንህ ነው በሰው ምርጫ የምትገባው ? አንተ ቀሚስ ትወዳለህ እና ሰው ሁሉ ቀሚስ መልበስ አለበት? እኔ ያልኩት ይሁን ማለት ትገቢ ነው? ሰው እርቃኑን ቢሄድ አንተን እስካልደረሰብህ ድረስ መብቱ ነው ። ” አልኝ ሌላኛው የልቤ ወገን።

“ባህላችን ይፈቅደዋል ? ሐይማኖታችንስ ? ሌላው ቢቀር የሴት ገላ ለሰው አይን መገለጡ ተገቢ ነው? ቀሚስ ወይም ሌላ የሴትን ገላ የሚሸፍን ነገር ቢለብሱ አይሻልም? ” አልኩት ለተቃረነኝ የልቤ ክፍል ።

የሁለት ዓለም ሰዎች

“ባህል ባህል አትበል ባክህ ። ሰው የሚያደርግው የለመደውን ነገር ነው ። ያንተ ቤተሰብ ለሴት ልጅ ሱሪ ላያለብስ ይችላል ። አንዳንዱ ቤተሰብ ግን ልጁን ሲያሳድግ ሱሪ እያለበሰ ነው ። ታዲያ ያች ልጅ እንዴት ነው ሱሪ መልበስ ትክክል አይደልም የምትላት? የምታውቅው ሱሪን ነው ። እንዳውም ከጨቅላነቷ ሱሪ እየለበሰች ላደገች ሴት ስህተቱ ቀሚስ ወስጥ ገላን መሸሸግ ነው።”

የምመልሰው አልነበረኝም ።

አለባበሷ ሞቾት ስላልሰጠኝ ሁለት ዳቦ ለመብላት የነበረኝ እቅዴን ሰርዤ ባይበላ ፤ ባይጠጣ እያልሁ ጨረኩ ።

“ሂሳብ ስንት ነው?” አልኩኝ ሶስት የአስርብር ኖቶችን ከኪሴ እየሳብኩ ።

“ሃያ አምስት።”

ሰላሳ ብሩን ሰጥቼ አምስቴን ብር እየተጠባበቅሁ እያለ፡

“ይሄ ብቻ ነው ያለህ?”

የሁለት ዓለም ሰዎች

ግራ ገብቶኝ ምን ለማለት እንደፈለገች ለማገናዘብ ስሞክር፡

“ይሄ ብቻ ብር ካለህ እኔ ሐያ ብሩ ይበቃኛል ” አለችኝ አስሩን ብር ወደኔ እየመለሰች ።

“ኧረ አለኝ ሌላም ” አልኳት ተገርሜ ።

“ሌላ ብር አለህ?” አለችኝ በድጋሜ’

“አዎ አለኝ። “

አምስቴን ብር ተቀብዬ ተመለስኩ ።

እግዚያብሄር ችኩል ፤ ተሳዳቢ ፤ ክፉ ሰው ያሳይህና አይ ሰው ብለህ ሰውን ሁኩ ስትተች እጅግ ሩህ ሩህ ፤ ለሰው አሳቢ፤ የሰው ችግር የሚረዳ ሰው አሳይቶ ለሰው ተስፋ ከእግዝያብሄር በታች ሰው እንደሆነ ያስተምርሐል።

የሁለት ዓለም ሰዎች

ወስብሐት ለእግዚያብሔር!

ጸሐፌ ወዘገብሄ እሱባለው መዐመር