ስላንቺ ነገርስ አለም በታዘበ ጠቢብ በተቀኜ፤
ዝግታሽ ርጋታሽ ትልቁ ዝምታሽ እኔን እንዳሞኜ።
ባላምን መውደድሽን
ብከስ ተግባርሽን ማን ይፈርድብኛል ?
አኩርፌ ብጠፋ
ከውስጤ ብከፋ ማን ይጠይቀኛል?
ጥያቄ ሳነሳ ለምን ይሆን ብዬ
ፊትሽን ከነሳሽኝ፤
ስህተት ሰርተሻል እያልኩ ስናደድ
ስህተት አንተ ካልሽኝ ፤
ማነው የሚጠይቅ አትችልም የሚለኝ ?
ማኩረፍ ይቅርና የመካድ መብት አለኝ ።
ተይው በቃ መልሱን ፤
ልርሳው መጠበቁን ፤
ለጥያቄዬ መልስ መስጠቱ ይቅርና ፤
በመጻፍ ላበደ በመግጠም ለፀና፤
ደብዳቤ ለሚልክ እያነባ ፅፎ፤
መትማመን ላጣ ስብዕናው ተገፎ፤
በምን ጥፋቱ ነው ግምጫ የሚደርሰው
የላከው መልዕክቱን አንባቢ የተወው።
ጥፋቱ የእርሷ ነው ዝም ብላ ቀርታለች በሚል ሳጉረመርም
ያንን አስመልክቶ ለራሴ ሳወራ ወይ ደግሞ ስገጥም ፤
አንቺ እንደተከፋሽ ልቤ ይነግረኛል ፤
ይቅርታ ልጠይቅ ወይ ዝምታን ልመርጥ ግራ ይገባኛል፤
በኋላ ቆይተሽ ኩርፊያ አልደረሰኝም ስትይ ይሰማኛል ።
እሱባለው ቸኮል